የአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት የፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደጥናት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ አዲሃቂ ካምፓስ አዳራሽ ውስጥ አካሄደ
በዛሬው ዕለት ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. የአፍሪካ ሴቶች ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት “የኢትዮጵያ ሴቶች ሰላምና ደህንነት አጀንዳን በተጠናከረና አካባቢያዊ በሆነ መልኩ የመገንባት ፕሮጀክት” በሚል ርእስ ያዘጋጀውን የፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደጥናት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ አዲሃቂ ካምፓስ አዳራሽ ውስጥ አካሂዷል።
በቀጥታ ከአዲስ አበባ በዙም የተሳተፉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር አምባሳደር ቆንጂት በመክፈቻ ንግግራቸው፣ “የዛሬው ፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደ ጥናት፣ በፕሮጀክቱ ዓላማ፣ ይዘትና አቅጣጫ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የየድርሻችንን ኃላፊነት ለማወቅ የሚያስችል እንደሚሆን አምናለሁ። የመንግሥት አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ አመራሮች፣ ምሁራንና የማህበረሰብ ተወካዮች በሙሉ፣ ፕሮጀክቱ ቀጣይነት ያለውና መሬት የወረደ የሰላም ግንባታ ጥረት አጋዥ ተግባር የሚከናወንበት እንደሆነ ተገንዝባችሁ፣ ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት የበኩላችሁን አስተዋፅዖ እንድታደርጉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ” ብለዋል። የኢንስትትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤልም የጉባዔው ተሳታፊዎችን አመስግነው መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
ጉባዔው ቀጥሎ፣ የኢንስትቲዩቱ ምርምር ኃላፊ አቶ ማንይንገረው ሸንቁጥ የአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት አመሠራረትና ስለሚያከናውናቸው ተግባራት አጭር መግለጫ ከሰጠ በሁዋላ፣ የፕሮጀክቱ መሪ የሆኑት ወ/ሮ ማህደር ዳዲ ደግሞ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል። በመቀጠልም የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁር የሆኑት ዶክተር ገብረ ኢየሱስ፣ የአገራችን ሴቶች ግጭትን የመከላከልና የመፍታት የዳበረ ባህል እንዳላቸው ገልፀው፣ ይህንን እምቅ ባህላዊ አቅም ግን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማጎልበት እንደሚገባ አብራርተዋል።
መድረኩ ለውይይት ክፍት ተደርጎ ከተሳታፊዎች የተለያዩ አሳቦች ተሰንዝረዋል። በዚህም የትግራይ እናቶች ሰላምን የሚሹ ስለመሆናቸው፣ ከጦርነት ጉዳት ማገገም ሳይጀመር አሁንም ሌላ ስጋት እየተሰማቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
በመጨረሻም የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስና ቋንቋዎች ምክትል ዲን የሆኑት ዶ/ር ፀሃይ ገብረ ኢየሱስ ሴቶች ግጭትን የመፍታት እምቅ ችሎታ ቢኖራቸውም፣ ተሳታፊነታቸው አናሳ መሆኑን ገልፀው፣ ተሳታፊነታቸውን ማጎልበት ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም፣ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ 1325 ተፈፃሚ በማድረግ ለችግሩ መዋቅራዊ መፍትሄ እንዲሰጥ፣ በመዝጊያ ንግግራቸው መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

Views Today : 4
Views Yesterday : 2
Views This Month : 96
Views This Year : 1512
Total views : 1757