የአፍሪካ ሴቶች ሰላም እና ደህንነት ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶች፣ ሰላም እና ደህንነት አጀንዳ ዙሪያ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ እውቀትን እና የፖሊሲ ውይይትን ለማጎልበት ያለመ ሁለተኛውን ዓመታዊ የምርምር አውደ ጥናት፣ ነሐሴ 2 ቀን 2018 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በታሪካዊዉ ሴኔት አዳራሽ አካሂዷል።
አውደ ጥናቱም “የኢትዮጵያ ለሴቶች የሰላምና ደህንነት አጀንዳ በተጠናከረና አካባቢያዊ በሆነ መልኩ አተገባበርን እና የመቋቋም አቅምን መገንባት” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል። አውደ ጥናቱ በዋናነት በአካዳሚው፣ በመንግሥት ተቋማት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በሴት የሰላም ግንባታ ባለሙያዎች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም በምርምር፣ በፖሊሲ እና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ያለመ ነውም ተብሏል፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋና ዋና ዓላማዎች ለሀገራዊ ዕውቀት፣ ለፖሊሲ ተሟጋችነት እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች፣ የሰላምና የደህንነት አጀንዳን ተግባራዊ ለማድረግ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ቁልፍ ግኝቶችንና ምክረ-ሀሳቦችን መመዝገብን ያካትታሉ። በተጨማሪም በሰላም ግንባታ እና በግጭት መከላከል ሂደት ውስጥ የሴቶችን ትርጉም ያለው ተሳትፎ የሚያጠናክሩ ፖሊሲዎችን፣ ፕሮግራሞችን እና የወደፊት ጥናቶችን ለማገዝ የሚያስችሉ ተግባራዊ ምክረ-ሀሳቦችን እንደሚያመነጭ ይጠበቃል።
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ሴቶች የሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል ኢንስቲትዩቱ ሴቶች በሀገር አቀፍ ብሎም በአህጉራዊ የሰላም ውይይቶች ላይ ሴቶች ያላቸውን ንቁ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ፣ እንደ ቁልፍ የሰላም ግንባታ ባለድርሻ አካላት ያላቸውን አቅም ማጎልበቱን እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተዉ ተናግረዋል።
የምርምር ውጤቶችን ለመለዋወጥ፣ ትብብርን ለማጠናከር እንዲሁም ለፖሊሲ እና ለተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ግብዓት የሚሆኑ እውቀቶችን መፍጠርን ለማበረታታት ሲባል ተመራማሪዎችን፣ ባለሙያዎችን እና ፖሊሲ አውጪዎችን በአንድ ላይ አውደ ጥናቱ አሰባስቧል፡፡

Views Today : 1
Views Yesterday : 4
Views This Month : 97
Views This Year : 1513
Total views : 1758