በዛሬው ዕለት ሚያዚያ13 ቀን 2018 ዓ.ም. የአፍሪካ ሴቶች ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት “የኢትዮጵያ ሴቶች ሰላምና ደህንነት አጀንዳን በተጠናከረና አካባቢያዊ በሆነ መልኩ የመገንባት ፕሮጀክት – ሁለተኛ ምዕራፍ” በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን የፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደጥናት በኦሮሚያ ክልል ነቀምት ከተማ፣ ሴናፍ ሆቴል አዳራሽ ውስጥ አካሂዷል።
አውደጥናቱ ከመጀመሩ በፊት በቅርቡ በሕይወት ለተለዩን የኢንስቲትዩቱ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ክብርት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡
በቀጥታ ከአዲስ አበባ በበይነ መረብ የተሳተፉት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር አምባሳደር ታደለች ኃ/ሚካኤል በመክፈቻ ንግግራቸው፣ “የዛሬው ፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደ ጥናት፣ በፕሮጀክቱ ዓላማ፣ ይዘትና አቅጣጫ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የየድርሻችንን ኃላፊነት ለማወቅ የሚያስችል እንደሚሆን አምናለሁ። ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት በአዳራሹ ውስጥ በመገኘት ድጋፋችሁን ያሳያችሁን ኃላፊዎችን ማመስገን እወዳለሁ” ብለዋል።
ጉባዔው ቀጥሎ፣ የኢንስትቲዩቱ ምርምር ክፍል ኃላፊ አቶ ማንይንገረው ሸንቁጥ የአፍሪካ ሴቶች ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት ስለሚያከናውናቸው ተግባራትና አመሠራረት፣ እንዲሁም ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በመቀጠልም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ዞን አስተዳደሪ አቶ ዋቅጋሪ፣ “በኦሮሞ ማህበረሰብ አደስንቄዎች ለሰላም የሚያደርጉት አስተዋፅዖ ስላለ፣ የአፍሪካ ሴቶች ሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዩት የያዘውን ዓላማ የሚያግዝ ማህበራዊ ሃብት አለን” ብለዋል “ስለሰላም መሥራት የጋራ ጉዳያችን በመሆኑ ከጎናችሁ መሆናችንን ለመግለፅ እወዳለሁ” በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡ በመድረኩ ሌሎች የዞኑ አስተዳደር የመንግሥት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ከዛሬ ሚያዚያ 13 ቀን 2018 ዓም. ከሰዓት ጀምሮ፣ ከክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ተሳታፊዎች ለሚቀጥሉት አራት ተከታታይ ቀናት ሥልጠናው የሚሰጥ ይሆናል፡፡





Views Today : 1
Views Yesterday : 4
Views This Month : 97
Views This Year : 1513
Total views : 1758